አዲስ ዓመትን በማስመልከት ቦረና ዩኒቨርሲቲ በያቤሎ ከተማ ለሚገኙ ድጋፍ የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች የበዓል ገበታ ድጋፍ አደረገ

Share this post on:

ቦረና ዩኒቨርሲቲ፣ ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም

ቦረና ዩኒቨርሲቲ አሮጌው ዓመት ተጠናቆ አዲሱ ዓመት የሚቀበሉበት ዋዜማ የሆነውን የጳጉሜን 5 “የነገ ቀን” እና መጪውን አዲስ ዓመት በማስመልከት፣ በያቤሎ ከተማ ለሚገኙ ድጋፍ ለሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች የበዓል ገበታ ድጋፍ አበርክቷል።

ይህ የ“ነገ ቀን” መርሃ ግብር ዛሬ ላይ ሆነን ለነገው ትውልድና ለሀገር ብልጽግና በዕቅድ፣ በእውቀትና በትጋት መሥራት እንዳለብን ለማመላከት ያለመ ነው። ዩኒቨርሲቲው ይህንን ዓላማ ሰንቆ በበዓሉ ዋዜማ ያበረከተው የዱቄትና የምግብ ዘይት ልገሳ ድጋፍ ለሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች የበዓል ገበታ ለማገዝ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በዕለቱ በተካሄደው የድጋፍ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የቦረና ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኩላ ጅሎ፤ ዩኒቨርሲቲው መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ የበዓል ደስታን ለማጋራት በያቤሎ ከተማ ለሚገኙ ድጋፍ ለሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች የበዓል ገበታ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። አክለውም ዩኒቨርሲቲው በተጠናቀቀው የ2018 የሥራ ዘመን በርካታ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፣ በቀጣይም የማኅበራዊ ተደራሽነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በመጨረሻም መጪው አዲስ ዓመት ለሁላችንም የሰላምና የጤና ዓመት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቦረና ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ጡነሌ ጎዳና በበኩላቸው፤ ቦረና ዩኒቨርሲቲ በዋዜማው ላደረገው የላቀ የበጎ አድራጎት ሥራ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ በጽሕፈት ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የበዓል ገበታው ተጠቃሚ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎችም ዩኒቨርሲቲው በዋዜማው ያደረገላቸውን ወቅታዊ ድጋፍ ከልብ አመስግነዋል።

ቦረና ዩኒቨርሲቲ በተጠናቀቀው የ2018 የሥራ ዘመን የማኅበረሰብ አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ከተከናወኑት ዋና ዋና ሥራዎች መካከል፦

ለ2,800 ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ፣
ለተማሪዎች አገልግሎት የሚውሉ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች (ዴስኮች) ማበርከቱ፣
ለ6 የመንግሥት ተቋማት የኮምፒውተር ድጋፍ መስጠቱ፣
በቦረና ዞን በሚገኘው 14 ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የንቅናቄ (Motivation ) ሥልጠናና የክረምት ቲቶሪያል (የክለሳ ትምህርት) ፕሮግራም ማቅረቡ፣
ለመምህራንና ለትምህርት ባለሙያዎች የፔዳጎጂ አሰልጣኞች ሥልጠናና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወኑ፣
እንዲሁም ድጋፍ ለሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች የቤት እደሳና ግንባታ ማከናወን፣ እንዲሁም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታን ማጠናቀቅ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ ለመወጣትና የትምህርት ልማትን ለማበረታታት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስታውቋል።

​”Dedicated to Resilient Pastoral Future”

ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ

Share this post on:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *